ስለጊዜያዊው ሁኔታ መግለጫና ለመንግሥትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ

by Bruck Tl
0 comment

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰባዊ ድርጅቶች ኔትዎርክ ከ50 በላይ የሆን ተቋማት ስብስብ ነን። ስብስቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና እድገት፤ የሕዝቧን ሠላም፤ ደኅንነትና አንድነት ለመጠበቅና ለማጎልበት በቅርቡ የተቋቋመ ዓለም-አቀፋዊ የትብብር አውታር ነው። በቅርቡም በኅዳሴ ግድብ ላይ ያለንን ጠንካራ አቋምና የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል በማውገዝና ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን በመመኘት መግለጫዎች አውጥተናል። 

የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በኢዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ ዘርና ሃይማኖት ላይ ያተኮረ አሰቃቂ ግድያ፣ የንብረት ማውደምና ዝርፊያ መፈጸሙ አምርሮ ኣሳዝኖናል፤ ዘግኖናል፤ አሳፍሮናልም። ስለሆነም ይኸንን ኢሰብአዊ፤ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን። በዚህ ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖቻችን ቤተሰቦችና ወዳጆችም መጽናናትን እንመኛለን። 

ኢትዮጵያ የልዩ-ልዩ ብሔረሰቦችና የተለያዩ ሐይማኖቶች ያሏቸው ዜጎች ለዘመናት በመተሳሰብ፣ በመጋባትና በመከባበር የኖሩባትና በጋራ ታሪካቸው የበለጸገች አገር መሆኗ ይታወቃል። እኝህ አሸብራቂ እሴቶችና ማንነቶች ያሏቸው ዜጎቿ በመተሳሰብና በመተባበር የኖሩና አገራቸውን የደፈሩ ጠላቶችን እንደ አንዲት አገር ሕዝብ በጋራ ተሠልፈው በከፈሉት የጋራ መስዋዕትነት እያሳፈሩ በመመለስ ኢትዮጵያችን ነፃነቷን አስከብራ እንድትኖር ያስቻለ አኩሪ ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸው የታወቀ ነው። 

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የትኛውንም ብሔር ወይም ሐይማኖት የማይወክሉና የፖለቲካ ሥልጣንና የሃብት ማካበት ፍላጎት ያሰከራቸው ፅንፈኛ ቡድኖች በአገራችን ላይ የጥላቻና የመለያየት መርዝ እየረጩ መገኘታቸው በዜጎች መሃል የቆየው ትሥሥር እንዲላላና በመሃላቸው ልዩነት እንዲሰፋ መደረጉ የሕዝባችንን አንድነት በእጅጉ ፈተና ላይ ጥሎት ይገኛል። በዚህም ምክንያት ወጣቱ ድምፃዊ ሃጫሉ ከተገደለበት ምሽት ጀምሮ እነዚህ እኩይ ዓላማ ያላቸው ፅንፈኛ ቡድኖች ዛቻቸውን ተግባራዊ በማድረግ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ አካባቢ ንጹሃን ኢትዮጵያውያንን በማንነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁናቴ በመገደላቸውና፤ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ንብረታቸውንም እንዲወድም መደረጉን መስማታችን በጣም አሳዝኖናል፤ አስቆጥቶናልም። 

እነዚህ የጥፋት ቀስቃሾችና ተካፋዮች በምንም ዓይነት የኦሮሞን ሕዝብ ይወክላሉ ብለን አናምንም። አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ አብሮ የመኖር ባህሪውን አሁንም እያሳየ ነው። በሁሉም ጥፋት በታየባቸው አካባቢዎች ቤታቸው በመቃጠሉ መሄጃ ያጡ ተጠቂዎችን በየቤታቸው ደብቀው ከሞት ያዳኑ የኦሮሞ ተወላጆችን ኢትዮጵያዊና ሰብዓዊ ተግባሮች እንደምሳሌ መጥቀሱ አስፈላጊ ነው። በዚህ ወገናዊና ሰብዓዊ ተግባራቸውም የጥፋት ኃይሎቹ እነሱን እንደማይወክሏቸው በተግባር አስመስክረዋል፤ እኛንም ሆነ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አኩርተዋል። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ሁከቶች ተከስተዋል። ንፁኃን ዜጎች ያለ ጥፋታቸው ሲገደሉ፤ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ሲጣሉና፤ ንብረታቸውም ሲዘረፍ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስከበር ተመጣጣኝና አፋጣኝ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠቡ የጥፋት ኃይሎቹ ሕገ-ወጥ ተግባራቸውን እንድቀጥሉበት አበራቷቸዋል ብለን እናምናለን። 

መንግሥት የሃገራችንን ህልውና ለማስጠበቅ፤ ሕግ ለማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሰሞኑን በመውሰድ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪና አበራታች ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም፣ መንግሥት የጀመረውን የሕግ የበላይነትን የማስከብር፤ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅና ወንጀለኞችን ለፍትኅ የማቅረብ እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ ግዛት በሠላም ሠርቶ የመኖር ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲረጋግጥና ዋስትና እንዲያገኝ እያሳሰብን፤ 

1. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለመደ አስተዋይነቱ እና ሚዛናዊነቱ ላይ በመመርኮዝ አንድነቱን የሚያደፈርሱና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ ፅንፈኞችን ለይቶ በማወቅ አሁንም አብሮነቱን እንዲያጎለብትና የጋራ ጠላቱን እንዲከላከል ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። 2. ከየመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በየቤተ እምነቱና በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖቻችን ከመንግስትና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመረባረብ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ በተለያየ መንገድ ለማድርግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን። 3. ሰሞኑን በአዲስ አበባ፣ በሻሸመኔ፣ በዙዋይ፣ በኮፈሌ፣ በባሌ ሮቤ፣ በጎባ፣ በአሰላ፤ በአምቦ፤ በጂማ እና በሌሎችም ከተሞችና ቀበሌዎች ውስጥ በግድያና ንብረት በማውደም ወንጀል ተሳታፊ የሆኑትንና የቀሰቀሱትን ሁሉ ባፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። 4. ኅብረተሰብ በኅብረተሰብ ላይ የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎች በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ በማሰራጨት ግጭቶችን የሚያስተባባሩና የሚመሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነቅቶ እንድጠብቅና ከመካክሉም ለይቶ በማውጣትና ከመንግሥት ጋር በመተባበር በሕግ ፊት የራሱን አስተዋፅ እንዲያደርግ እናበረታታለን። 5. በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ለዚህና ከዚህ ቀደም በተከሰቱት እኩይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ፤ ድጋፍ ያደረጉና በህግ የተጣለባቸውን የህዝብን ስላምና ደህንነት የማስከበር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ባለሥልጣናትና የመንግሥት ሠራተኞች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማጠናቀቅና እርምጃ በመውሰድ መንግሥት ሃልፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን። 6. ኅብረተሰብን ከኅብረተሰብ ጋር ለማጋጨት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩ መገናኛ-ብዙኃንና /ሚዲያዎች/ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ እርምጃ እየደገፍን የፍርድ ሂደቱም ግልጽ፤ ፍትኃዊና ተዓማኝነት እንዲሆን እናሳስባለን። 7. በውጭ ሀገር የሚኖሩና ኅበረተሰብ በኅብረተሰብ ላይ እንዲነሳ ግጭት የሚቀሰቅሱ መልክቶችን በማኅበራዊ ሚድያ የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ከመንግሥት ጋር በመተባበር በውጭ አለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ለምንኖርባቸው የየሀገራቱ መንግስታት በማስገንዘብና በማጋለጥ ይህን እኩይ እንቅስቃሴ ለመግታትና ለማስቆም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። 8. መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍትኅ ለማቅረብና የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሰብዓዊ መብት ጥሠት፤ ለፖለቲካ ወገንተኝነትና ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ፤ ተፈጥሮ የነበረውን የፖለቲካና ሲቪክ ተሳትፎ ምኅዳር እንዳያጠበው ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። 

በመጨረሻም እኛ ከ50 በላይ የምንሆን በመላው ዓለም ተሰራጭተን የምንገኝ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ- ኢትዮጵያውያን የሲቪክ ድርጅቶች፤ መንግሥት ለሚወስደው ሕጋዊ እርምጃና በዓባይ ጉዳይ ላይ እየወሰደ ላለው ቆራጥና ትክክለኛ አቋም እስከአሁን ድረስ እያደረግን ያለውን ተካፍሎ ለማጠናክር ዝግጁ መሆናችንን በድጋሜ እንግልጻለን። 

ዓባይና የኅዳሴ ግድብ ኅልውናችን ነው! የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን ይፈቱ! ግብፅ በኢትዮጵያ ጥያቂዎች ላይ ጣልቃ መግባቷን ታቁም! ኢትዮጵያ በአንድነቷ ፀንታ ለዘላለም ትኑር! 

related posts

Leave a Comment